ቶሮንቶ፤ ካናዳ
የወያኔ ፉከራ የኢትዮጵያን ሰማይ አጣቧል። የደርግን ሠራዊት እስከ አፍንጫው ቢታጠቅም ደምሠነዋል፤ የደርግን ጄኔራሎች በድንጋይ ማርከናል (ጌታቸው ረዳ)፤ ስድሳ ሺህ ሰው ሰውተናል፤ ኢትዮጵያን ያገኘነው ወይም ወደ ሥልጣን የመጣነው በከፈልነው ደም ነው፤ የጀግኖች ጀግና ነን፤ በሳት የተፈተን “ወርቅ” ነን፤ በወርቅነታችን እንኮራለን፤ ወዘተ.. ይላል ወያኔ።
ለከፈልነው የደም ዋጋ ክበጌምድርና ሰሜን ጎንደር ወልቃይትን፡ ጠገዴን፤ ጸለምትን ወስደናል። አርማጭሆ፤ ሰሜን ራስ ዳሽንን እና ላሊበላን በክልላችን መልክዓምድር (ጂኦግራፊ) አስገብተናል። ወደፊት ተግባራዊ ይሆናል።
ከወሎና ከአፋር የምንፈልጋቸውን ለም አካባቢዎችን ወስደናል፤ በድል አድራጊነነት ወደ መሃል ኢትዮጵያ ስንገሰግስ የሀገሪቱን ባንኮች፤ ከተሞች፤ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶችን ሳይቀር ዘርፈናል፤ የግል ቤቶችን እየሠበርን፤ የሴቶች ጉትቻ ሳይቀር ቀምተናል፡ መኪናዎችን ቀምተናል (የቀድሞ ዲፕሎማት መኪናውን መቀማቱን ለዚህ ጸሃፊ ነግሮታል)፤ ጎንደር ስንገባ የድል አድርዳጊነታችን ምልክት እንዲሆን ጣሊያን የተከለውን ብቸኛውን የመብራት ሞተር፣ አልነቀል ብሎ ያስቸገረንን ነቅለን ወደ አገራችን የተከዜን ወንዝ አሻግረን ወስደናል። የጎንደር ከተማ በጨለማ እንድትዋጥ አድርገናል።
በጎንደር ከተማ ወደ አርባ ኪሎሜትር እርቆ ጣሊያን ሲለቅ ትቶት የሄደውን፤ አገሬው እንደመታሰቢያ የሚያየውን የመንገድ መሥሪያ” መዳመጫ ወስደነዋል። ከፈረንጅ አገር ወደ አገራቸው ቤተሰብ ለመጠየቅና በኢትዮጵያ ያመጣነውን “ነጣነት” ለማየት የመጡትን ግለሰቦች በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያና በሌሎቹ ከተሞች ሻንጣቸውን እየከፈትን የምንፈልገውን ዕቃ ዘርፈናል፤ ገንዘባቸውን በብዙ ሺዎች የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር ቀምተን ወስደናል፤ የእኛ ደጋፊዎች የሆኑ “ወያኔዎች” የቀረጥ ታክስ ሳይከፍሎ ከውጭ አገር ልዩ ልዩ እቃዎችን እያስገቡ እንዲሸጡ እና ነባሩ ነጋዴ እንዳይፎካከራቸው አድርገን፤ በተለይ በአዲስ አበባ ነጋዴውን የጉራጌ ብሄረሰብ ከንግድ ዓለም አስወግደን ንግዱ “በወያኔ “ ሰዎች እጅ እንዲሆን አድርገናል።
የአዲስ አበባን ከተማ ኑዋሪ ሕዝብ ቦታና ቤት ለልማት ይፈለጋል እያልን እንዲለቁ አስገድደን የምንፈልጋቸውን ቦታዎችና ቤቶች የ”ወያኔ” ሰዎች ሃብት እንዲሆን አድርገናል። ከተማዋን ከቆረቆሩት ከምኒልክና ከጣይቱ ዘመን ጀምሮ ከልጅ ወደ ልጅ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአዲስ አበባን ህብረተሰብ በትነነዋል። በሰንበቴ፤ በዕቁብ፤ በክርስትና ፤ በዕድር፤ ሲገናኝ የነበረውን፤ በተለይ የአዲስ አበባን ህብረተሰብ በትነን ድምጥማጡን አጥፍተናል።
በአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች፤ ፎቆች፤ አፓርትመንቶች በልጆⶫችን፤ በሚስቶቻችንና በድብቅ ሰዎች ስም ከባንክ ከወለድ ነጻ የሆነ ገንዘብ እየወሰድን፤ እየቀማን ሠርተን ከተማዋን ፎቅ በፎቅ አድርገን “ኪራይ ሰብሳቢዎች” ሆነናል። ታላላቅ ሆቴሎች ከኢትዮጵያ ባንክ ገንዘብ እየወሰድን በድብቅ ስም፤ በልጆቻን በሚስቶቻችን፤ እንዲሆም ከውጭ አገር ዘራፊዎች ጋር እየተስማማን ሠርተን አዲስ አበባን ኒዮርክ አድርገናል፤ ከውጭ አገር ዘራፊዎች ጋር እየተስማማን የተለያዩ ፋብሪካዎች መሥርተን የወያኔና የደጋፊዎች ንብረት ሆነዋል። የኢትዮጵያን ለም መሬቶች ለፖለቲካ ፍጆታ እና ለግል ጥቅም ለአረቦች፤ ለህንዶች እና ለሌሎች ባለጸጋዎች ሽጠን የምናገኘውን ትርፍ ወደ ውጭ ሀገር አሸሽተናል። ለፖለቲካችን እንዲያመች በማለት ከሱዳን ጋር ተስማምተን የአማራውን አገር መሬት (ጎንደር) ለሱዳን በነጻ ሰጥተናል። የዮሐንስ ደም የፈሰሰበት መሬት በኢትዮጵያ ታሪክ እንደገና እንዳይነሳ አድርገናል። የአድዋ ሰው ስላልሆነ ጉዳያችን አይደለም። ለእኛ ከዮሐንስ አንገት መሰየፍ የመሃዲ አገር ሱዳን ይበልጥብናል። ዮሐንስ ከአማራ ጋር የተጋባ የአማራ ንጉስ እንጅ የእኛ አይደለም፡፡
ለጅቡቲ መንግሥትም የተለያየ ጉቦ እንደ ሱዳን የመሬት ጉቦ ባይሆንም እጫት በገፍ ከማቅረብ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እየቀማን መብራት በሽያጭ መልክ እንሰጣለን። የሚገኘው ገንዘብ ወደ ኪሳችን ይገባል። የልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ፕላን ለዓለም ባንክ እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪዎች፤ ለባለጸጋ መንግሥታት መንገድ፤ ድልድይ፤ የጤና ጥበቃ ተቋሞች፤ ትምህርት ቤቶች እንሠራለን እያልን በኢትዮጵያ ስም ወደ አምሳ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተቀብለን ግማሹን ወደ ኪሳችን አስገብተን በተለያዩ የውጭ አገር ባንኮች በሚስቶቻችን፣ በልጆቻችን፤ በዘመዶቻችን ስም አስቀምጠናል። በእንግሊዝ፤ በአሜሪካና በካናዳ ቤቶች ገዝተን እናከራያለን። ባንዳንዶቹም ቤተሰቦቻችን ይኖሩባቸዋል።
በመላ ኢትዮጵያ የተቋቋሙት፤ ፋብሪካዎች፤ የእርሻ ልማቶች፤ የአበባ ተክሎች፤ የግመልና የአህያ እርባታ ሳይቀር የእኛና የሽርከኞቻችን የውጭ አገር ባለሃብቶች ንብረቶች ናቸው። መንገድ ሥንሠራ አሸዋ፤ ስሚንቶና ብረት አቅራቢዎቹ፤ ስሚንቶ በጥባጭዎቹ፤ አፈር ዛቂዎቹ፤ ልዩ ልዩ የህንጻ ቁሳቁስ፤ ቤንዚልና ናፍጣ አቅራቢዎቹ ፤ ሠራተኞቹ ኩሊዎች እና አለቃዎቻቸው የእኛ “የወያኔ” ሰዎች ናቸው። ከፕሮጀክቶቻችን በሁለተኛ እና በሦስተኛ ደረጃ ለደጋፊዎቻችን ለሆዳሞቹ የአኦሮሞ፤ የአማራ፤ የአደሬ፤ ወዘተ ሰዎች ጠብ ጠብ እናደርግላቸዋለን።
ጥንታዊውንና ስኬታማውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወያኔ አየር መንገድ አድርገን አንድ ወያኔ ሥራ አስኪያጅ ፈላጭ ቆራጭ አምባገንነን አድርገናል። ሚስቶቻችንና ልጆቻችን ውሎ ገብ ዱባይ ሂደው ገበያ ገብይተው የሚመለሱት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አድርገናል።
በፖለቲካው ዓለም ፈረንጅን ሸውደነዋል። በተለይ አሜሪካንና ዓውሮፓን። እኛ ምን እናውቃለን ከጫካ የመጣን መሃይሞች አስተምሩን፤ የምንተማመነው በእናንተ በጌቶቻችን ነው፤ የዴሞክራሲን ሀ-ሁ አናውቅም፤ ለመማር ጊዜ ይወስድብናል፤ ታገሱን፤ ወደን አይደለም፤ የመማርና ያለመማር ጉዳይ ነው። በእናንተም እኮ ዴሞክራሲ ብዙ ጊዜ ወስዶባችኋል፤ በመቶ የሚቆጠር ዘመን፤ በእኛ ጊዜ ግን ከእናንተ ዴሞክራሲን በመገልበጥ በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲን እውን እናደርጋለን፤ ታገሱን ወደን አይደለም፤ እያልን ፈረንጅን በመሸወድ ኢትዮጵያን በተለይ አማራንና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ደቁሰንበታል። ሞኙ ፈረንጅ እውነት መስሎት የዶላር ዝናብ አዝንቦ ጎርፍ ሊወስደን እየተቃረበ ነው።
ንጥቁን ኃያል አገር ለማሳሳት ያልፈነቀልነው ደንጊያ፤ ያልጠረግነው መንገድ የለም። የኢሳያስ መንግሥት በሶማሊያ ገብቶ ሶማሊያን የሚያበጣብጠውን የአልሽባብን ድርጅት እየረዳ ነው፤ አልቃይዳ የሚባለውን ጠላታችሁን የሚረዱት የኤርትራ ሠርጎ ገቦች ናቸው፤ ጠላታችሁን አልቃይዳን እና አልሸባብን የእናንተ ደም ሳይፈስ በኢትዮጵያ ደም እንዋጋለን፤ ብቻ ገንዘብና የፖለቲካ ድጋፍ ስጡን፡ ሌላውን ለእኛ ተውት፤ እያልን ያልተደረገው ተደረገ፤ የተደረገውን አልተደረገም በማለት በውሸት ታላቁን ንጥቅ ኃያል አገርና ተባባሪዎቹን አገሮች ሸውደን እስካሁን በእነርሱ ሙሉ ድጋፍ በሥልጣን ላይ ኖረናል። ከእኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር እንዳይነጋገሩ አድርገናል። በእነሱ ቤት ከለእኛ ወያኔዎች ሌላ የፖለቲካ ድርጅት በኢትዮጵታ ሰማይ ክልል የለም። ለኃይለ ሥላሴ መንግሥት በሥልጣን ዘመኑ ያልሰጡትን ለእኛ በአንድ ዓመት ይሰጡናል፤ሟቹ መሪያችን “ፈረንጅ ሞኝ ነው” ያለው ያለምክንያት አልነበረም። ለዚህ ነው የንጥቁ ኃያል ሀገር ፕሬዚደንት ኢትዮጵያ የምትባለውን የእኛን ቅኝ ግዛት ሲጎበኝ “መቶ በመቶ በሕዝብ ድምጽ ተመርጠናል ያልነውን ተቀብሎ ያጸደቀው፤ ለታላቁ ኃያል አገር የፖለቲካ ጥቅም ስንል የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም የሸጥነውን ተቀብሎ “ኢትዮጵያዊያን ጥሩ ተዋጊዎች ናቸው፡ የእኛ ወታደሮች ደም አይፈስም፤ ኢትዮጵያዊያን ለእኛ እየሞቱ ነው ብሎ ያከበረን። ባደረግነው የንጥቁ ኃያል አገር እና የማዕራብን አገሮች የሶማሌ ሽወዳ ምክንያት አቅፎ ደግፎ አሳድጎ አዲስ አበባ ድረስ ያስገባን።
በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራውን የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ከምዕራብ ጋር አጣልተን አፍ እንዳይኖረው አድርገናል። በዚህም ሽወዳችን የአድዋን ሥርዎ መንግሥት መሥርተን ኢትዮጵያን በቆራጭ ፈላጭነት እንድንቆጣተር አድርጎናል። የትግራይ ጠላቶቻችን እንደርታን፤ ራያዘቦን፤ ተንቤንን ከጫወታ ውጭ አድርገን የፖለቲካ ተመልካች አድርገናቸዋል፡
በእኛ በአድዋ ሥርዎ መንግሥት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ካልሆኑ የፖለቲካ ጳጳሳችን አቦይ ስብሃት እንዳሥተማረን የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ፤ የትግራይ ሕዝብ ደግሞ የአድዋን ሕዝብ ይበላል፤ እንዳለው ይሆናል።
የሽወዳው ፈላስፋ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምዕራብንና አፍሪካን ከመሸወዱ የተነሳ ተቀባይነቱ የአፍሪካ ፕረዚደንት እንዲሆን አድርጎት በዓለም የፖለቲካ መድረክ ከታላላቆቹ አገሮች መሪዎች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ከእነሱ ጋር የሻምፓኝ ብርሽቆ አጋጭቷል፤ በዚህ ምክንያት የአሜሪካ ፕረዚደንት የደህንነት አማካሪ ሱሳን ራይስ የሟቹ የሽወዳው ፈላስፋ ጠበቃ ብቻ ሳይሆን የሽወዳው ተካፋይ እንድትሆን አድርጓታል።
አንዳንድ ጊዜ ስናስበው “የሽወዳው” ፈላስፋ የአድዋን ሥርኦ መንግግስት እንድንመሠርት ያበቃን ጠቅላይ ሚኒስትራችን በህይወት ቢኖር ኖሮ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ከአድዋ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ሰማይ ይጠቁርብን ነበር ወይ? በብዙ ድካምና ጥረት የተበተብነው የአማራና የኦሮሞ ጥላቻ ወደ ፍቅር ይለወጥ ነበር ወይ? እንድንሰማው የማንፈልገው የኢትዮጵያ ታላቅነት ይሰበክ ነበር ወይ? በሟቹ መሪያችንና በፖለቲካ ጳጳሱ በአቦይ ስብሃት የተተበተበው የጎሳና የሃይማኖት የከፋፍለህ፤ እያጣላህ ግዛ መንግሥታችን ከጥያቄ ላይ ይወድቅ ነበር ወይ? በኛ ጊዜ ተወልደው አድገው የተማሩት የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች የኛን የከፋፍለህ ግዛ ፍልስፍና አፈር ድሜ አስበልተው የወያኔን መንግሥት ይፈታተኑ ነበር ወይ?
ለእኛ የፖለቲካ ፍጆታና የገንዘብ ምንጭ እንዲሆን፤ ብሎም ኃያል አገሮች ጥሩ ይሠራሉ ብለው እንዲያምኑ እና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድጋፍ እንዲሰጡን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር እንቅልፍ ሳይተኛ በከፍተኛ ጥበብ ያመጣልን የዓባይ ግድብ ሥራ ከጥያቄ ውስጥ ይገባብን ነበር ወይ? ዓለምን ሸውዶ የወያኔን መንግሥት እውን ያደረገው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ካለእድሜው በአማራ ጥላቻ እና በዋልድባ መነኩሳት ጸሎት በአንድ አክራሪ የአማራ ሽብርተኛ በአበበ ገላው አስደንጋጭ ጥያቄ በተንኮል የተተበተበው የአንጎል ሥሩ ተበታትኖ ወደ መሬት መግባቱን ስናስብ የእኛ ውድቀት እየተቃረበ መሄዱ ይሰማናል። የአማራውን ሽብርተኛ አበበ ገላውን አንዷ ወያኔ እንዳለችው በሽጉጥ አንጎሉን መፈረካከስ ወይም በልዩ ዘዴ ወደ እትዮጵያ እንዲገባ አድርጎ ቴዎድሮስ ገዣችንን ደጃዝማች ንጉሴን ከተማችን አድዋ ላይ እንደሰቀለው አበበ ገላውንም አድዋ ላይ መስቀል ያስፈልጋል የሚሉ ደጋፊዎቻችን እየበዙ ሂደዋል። ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ሰማይ እየጠቆረ በመሄዱ ከዚህ የምንደርስ አይመስለንም።
ከዚህ በላይ በመጠኑ እንዳየነው የወያኒ የአስራ ሰባት ዓመት ትግል ድሃውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመዝረፍ፤ ለመቀማት፤ ለመሥረቅ፤ ለመግፈፍ ፤ ለመግደል፤ ለማሠር ለመደብደብ፤ ለማዋረድ ነው ማለት ነው። ወያኔ እንደሚለው ስድሳ ሺህ ሰዎች የተሰውትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት፤ ፍትህና እኩልነት ብሎም ለሀገራችን ብልጽግና ሳይሆን ከፍ ተብሎ እንደተዘከረው ለሥርቆት፤ ለመዝረፍ፤ ለመቀማት፤ ለጉቦ፤ ለአድሎ፤ ለኢፍታዊነት፤ ለዘረኝነት ከሆነ የፈሰሰው ደም ከንቱ ሁኗል ማለት ነው። እርግጠኛ ነኝ ሟቾቹ ሰዎች የወያኔ መሪዎች ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ እና እኩልነት የቆሙ እውነተኛ ሰዎች መስሏቸው ይሆናል። ዞሮ ዞሮ አማራ የትግራይን ሕዝብ ጨቁኖ ለድህነት ጥሎና እያሉ አስራ ሰባት ዓመት ለተከታዮቻቸው የወያኔ ወታደሮች ሲያስተምሩ የነበረውን የወያኔ ታጋዮች በአማራው አገር ሲገቡ “አማራ”፤ የተባለው ሕዝብ ከነሱ ባነሰ ሁኔታ በድህነት የሚገኝ መሆኑን ተገንዝበው፤ አንዳንዶቹም በመገረም መሪዎቻቸውን ለምን እንደዋሿቸው ጠይቀዋቸዋል። ፍሬ ነገሩ የተሰውት የስድሳ ሺህ ሰዎች ደም በከንቱ የፈሰሰ ሲሆን ለጥቂቶቹ ግን ደማቸው የገንዘብና የብልጽግና ምንጭ ሆኗል።
ወደ አርዕስቱ ተመልሰን የወያኔን ፉከራ ስናየው የአስራ ሰባቱ የወያኔ ውጊያ እንደሚያወራው ድል አድራጊው ወያኔ ብቻውን አይደለም። ብዙ ተዋንያኖች ሞልተውበታል። በዚህ ጽሃፊ አስተያየት ለመንግሥቱ ኃይለማርያም የድርግ መንግሥት ውድቀት እና ለኢትዮጵያ ሠራዊት ድል መመታት ሃምሳ በመቶ የሚሄደው ለሻዕቢያና ለውያኔ ጥምር ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የወያኔ ሚና ሃያ በመቶው ይመስለኛል። ሰላሳ በመቶው የወያኔ አለቃ፤ አስተማሪ፤ ለአዲስ አበባ መጠቃት ዋና ተዋንያን ለነበረው ለፕረሲደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይሆናል። ካለ እሳያስ ስድጋፍ የወያኔ አዲስ አበባ ገብቶ በዙፋን መቀመጥ የሚታለም አይመስለኝም። ለደርግ መንግሥት መመታት ሌላው አምሳ በመቶው ለተለያይዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሚሄድ ይመስለኛል። ከዚህ ውስጥ ለደርግ ሠራዊት መመታት የጦር ተቅላይ አዛዥ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአዛዥነት አለመብቃት፤ ጀኔራሎቹ የእሱ ታማኞች በነበሩ የበታች ሹማምንቶች እንዲያዙ በማድረግ ሞራላቸውን በመንካቱ፤ በመግደሉ፤ በመስደቡ፤ በጠቅላላ ጦሩን በመበወዙ እና ብቃት ባልነበራቸው ጀኔራሎች፤ እንደ ለገሠ አስፋው በመሳሰሉ እንዲመራ በማድረጉ፤ የሐረርን የጦር አካዳሚ ምሩቆች በመጨፍጨፍ ሃያ በመቶ ለእሱ የሚሰዋ ይመስለኛል። ሌላውን ሰላሳ በመቶ የኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ)፤ የኦሮሞ ነጻነት ንባር፤ ኢዲህ፤ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት)፤ ..ወዘተ.. የሚካፈሉት ይመስለኛል። ይህ ሳይንሳዊ ጥናት አይደልመ፤ ግምት ሲሆን ጸሃፊው ለመታረም ዝግጁ ነው። ፍሬ ነገሩ ለመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት ውድቀትና ለኢትዮጵያ ሠራዊት መመታት የወያኔ ፉከራ ጆሯችንን እንዳደነቆረው የእሱ ብቻ አለመሆኑን ለመጠቆም ነው።
ስለ መንግሥቱ ኃይለማርያም ፕረዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንደ ኢትዮጵያዊያን አቆጣተር በ1974 ዓ/ም ሱዳን በነበረበት ጊዜ ለኒዮርክ ታይምስ የሰጠው ቃለ መጠይቅ ትዝ ይለኛል። በቃለ መጠይቁ እንዲህ በሚል መልስ ነበር የተናገረው፡ “መንግሥቱ ኃይለማርያምን እኛ እንዲሞት አንፈልግም፤ የእሱ መኖር የእኛ ነጻነት ዋስትና ነው። እኛ የማናደርገውን እያደረገልን ነው። ብቃት ያላቸውን አደገኞቹን ሰዎች እየገደለልን ነው። ጦሩን ብቃት በሌላቸው ሰዎች እንዲመራ እያደረገልን ነው። ስለዚህ የእሱ መኖር የነጻነታችን ዋስትና ነው” ያለው በትክክል ሆኗል። ለዚህ ነው ለኢትዮጵያ ሠራዊት መመታት ጠቅላይ የጦር አዛዥ ዋና ተዋንያን ነው የተባለበት ምክንያት። እንደሚታወቀው የኮሎኔል መንግሥቱ መፈከር “እኔ ወይ ኢትዮጵያ” የነበረው ወደ መቶ አምሳ መኮንንኖች፤ ከነዚህ ውስጥ ዘጠና ጀኔራሎች እና ከፍተኛ መኮንኖች በመንግሥቱ ትእዛዝ እንደተገደሉ ተጽፏል። ለሻእቢያና ለወያኔ ከዚህ የበለጠ ድል የለም። እውነትም ኢሳያስ አፈወርቂ ለኒው ዮርክ ታይምስ የሰጠው ቃለ መጠይቅ በትክክል በሥራ ተተርጉሟል።
የመንግሥቱ ኃይለማርያም አለመብቃት በግልጽ የታየው “ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር” ተብሎ በእሱ አዛዥነት የተካሄደው “የቀይ ኮከብ” የኤርትራ ዘመቻ ውድቀት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በትግራይ በእሱ ቀኝ እጅ በሻምበል ለገሰ ይታዘዝ የነበረውን ጦር ካላንዳች ምክንያት የትግራይን ክፍለ ሀገር ለቆ ወደ ጎንደርና ወሎ እንዲሄድ አዞ ጦሩ ሲገሰግሥ በሻእቢያ መሪነት የተካሄደው “የእንዳ ሥላሴ ሽሬ” ጥቃት ነው። የመንግሥቱ ሃይለማርያምን ትዛዝ እውን ለማድረግ በጉዞ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ጦር በሻእቢያ መሪነት በድንገት አደጋ ጥለው ክፉኛ መትቶታል። በዚህ ድንገተኛ የሻእቢያ የወያኔ ጥቃት ወደ አሥር ጀኔራሎች ሲሞቱ ሁለት ሦስት ጀኔራሎች ተማርከዋል። ከነዚህ ውስጥ የሐረር አካዳሚ ምሩቅ ጀኔራል በርታ ጎመራው ይገኝበታል። ጀኔራል በርታ ጎሞራው ከተማረከ በሁዋላ ወያኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት የቆሙ፤ መንግሥቱ ኃይለማርያምና ደርግ ከተወገዱ በኋላ እውነተኛ ፍትሃዊ ዴሞክራቲክ መንግሥት የሚቋቋም መንግሥት እውን እንደሚሆን መስሎት ከሽሬ እስከ አዲስ አበባ በድል አድራጊነት ከገቡ በኋላ ጀኔራል በርታ ገሞራውን እና ሌሎች ወደ አሥር የሚሆኑ ከፍተኛ መኮንንኖች ወያኔ ከተጠቀመባቸው በኋል መረሸናቸውን የስብሃት ነጋ ወንድም የሐረሩ አካዳሚ ምሩቅ ኮሎኔል በላይ ነጋ ተናግሮ ወደ ላይኛው ዓለም ሂዷል።
The post የወያኔ ፉከራ ሲመረመር : ከበሪሁን አስፋው appeared first on The Ethio Sun.